“በአንድ ራስ ሁለት ምላስ”

ኢትዮጵያ ዛሬ-- ከፕ/ር ኤፍረም ይስሃቅ ጋር በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ኮስሞስ ክለብ የተደራደረው የነታማኝ ቡድን አባላት አበበ በለው በሚያራምደው ‘አዲስ ድምጽ ‘ ራዲዮ የማስተባበያ መግለጫ ለመስጠት ባደረጉት ሙከራ የበለጠ ጉዳዩን ሊደብቁት ወደማይችሉበት ደረጃ አደረሱት።
ይህ በሚስጢር የተካሄደው የድርድር ውይይት በመጀመሪያ በዚህ ድር ገጽ ሲወጣ እንዴት ታወቀ በሚል በነጻነት ሬዲዮ ቀርበው መግለጫ የሰጡት አቶ ታማኝ በየነ ሁኔታውን ቀላልና የሻይ ቡና ውይይት ነው ማለታቸው አይዘነጋም። ይሁንና እሁድ ታኅሣሥ 20 ቀን 2000 ዓ.ም አቶ አበበ በለው በሚያራምዱት ሬዲዮ ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ ስማቸው የተነሳው የኢትዮጵያን ሪቪው ድረ ገጽ አዘጋጅ አቶ ኤልያስ ክፍሌ፤ ታማኝ በየነ፤ ራሱ አበበ በለውና የኢትዮ ሚዲያ ድረ ገጽ አዘጋጅ አቶ አብርሃ በላይ ናቸው መገለጫውን የሰጡት።
ግለሰቦቹ በዚህ መግለጫቸው ድረ ገጹ በሰበር ዜናው ያመለከተውን ዜና አንድም ቦታ ሊያስተባብሉ ካለመቻላቸውም በላይ የበለጠ አብራርተውታል።ይኅውም በድረ ገጹ እንደተመለከተው የወያኔን ተልዕኮ ይዘው የመጡት ፕ/ር ኤፍሬም ይህንን የጀመሩትን “የሽምግልና” ሂደት በዲአስፖራው ለመቀጠል ይጠቅማሉ ወይም ያግዛሉ ካሉአቸው ግለሰቦች ጋር ለመደራደር የተጠራ ነበር። ጉዳዩ እነዚህን ግለሰቦች ተጠቅሞ የወያነን ፍላጎት በምን መልኩ ማሳካት ይቻላል የሚለውን እቅዳቸውን ለመግለጽ እንደነበር በተዘዋዋሪ አምነዋል። ይሀውም በሃገር ወስጥ የተጀመረው የወያኔን ገጽታ የመለወጥ ሴራ መሆኑን ማስተባበል ሳይችሉ ቀርተዋል።
አቶ ታማኝን ያስቆጣቸው ለምን ዜናው ወጣ? የሚለው እንደነበር ብዙዎች ቢገምቱም በዚህኛው መግለጫቸው ሊያስተባብሉ ቀርቶ በሚስጢር ይዘው የቆዩትን ሊያወጡ ተገደዋል። ታማኝ በነጻነት ሬዲዮ ቀርቦ እንዳለው ለስብሰባው ፕ/ሩ እርሱን የጠሩት ስለማይሳደብ ሳይሆን ሆነተብሎ የተቀነባበረ እንደነበረ አምነዋል። እንደውም ከወር አስቀድሞ የተሳትፎ ግብዣው ለተሳታፊዎቹ እንደደረሳቸውና አስፈላጊው የትራንስፖርትና የሆቴል ወጪያቸው እንደሚሸፈን ተገልጦላቸው እንደነበር አረጋግጠዋል። የኢትዮ ሚዲያው አዘጋጅ አቶ አብርሃ በላይ ግን ግብዣው እንደደረሳቸው በወቅቱ እንደማይመቻቸው ገልጾው ወዲያውኑ ማስታወቁን አልሸሸጉም።
በዚህ መግለጫቸው ቀደም ሲል በኢትዮ ቱዴይ ድረ ገጽ እንደተመለክተው ስብሰባው ሆቴል ጭምር ተይዞ በስፋት የተካሄድ እንጂ ታማኝ እንዳለው የሻይ ቡና ወግ እንዳልሆነ ሊሸሽጉ አልቻሉም። ይሁንና ግን ለምን በዚህ ደረጃ አሁንም ለመከራከር እንደፈለጉ ግልጽ ባይሆንም ዞሮ ዞሮ ተግባራቸውን ይበልጥ አጋልጠዋል። የአሁኑን መግለጫ ግለሰቦቹ ሲሰጡ ያረጋገጡትና ብዙዎችን ያስገረመው ሌላው ነጥብ ሰለፕ/ር ኤፍሬም የሰጡት ማብራሪያ ነው። ቀደም ባሉት ጊዚያት ግለሰቡ የወያኔ ተልዕኮ አራማጅ መሆናቸውን ሲናገሩ እንዳልቆዩ ሊያወድሱአቸው ቃላት ተቸግረው ሲታዩ ተስተውለዋል።”አገራቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ ናቸው፤ እርሳቸው ከጠሩ ያለማመንታት መሄድ ነው” በማለት ነበር አቶ ኤልያስ ክፍሌ ፕ/ሩን የገለጸው። ይሁንና የአቶ ኤልያስ ክፍሌ መጋበዝ ሰውን ስለማይሳደቡ ይሆን የሚሉ ታዛቢወች ብዙ ናቸው
አቶ ታማኝ “ ወያኔ ልሆን አስቤ ቢሆን እንኩአ ለምን የአንድ ቀን እድል አይሰጠኝም ?” በማለት ጉአደኞቼ ሲል የጠራቸውን የነጻነት ሬዲዮ አዘጋጆችን ወቅሰዋል። አቶ ታማኝ የፈለገው ምን አይነት እድል እንደነበረ በግለጽ ባያስቀምጥም ይህን የርሱንና አብረውት የነበሩትን ተናጋሪዎችን አስተያየት ያደመጡ ታዛቢዎች በቅርቡ ወዶ ወደ ወያነ ጎራ በተቀላቀለው ሰሎሞን ተካልኝ ላይ እነዚህ ሰዎች ሲያወርዱበት የነበረውን ውርጅብኝ በማስታወስ በራሳቸው ሲሆን ከሚሉት ጋር በማገናዘብ ግራሞታቸውን ሰንዝረዋል።
ሌላውና አስገራሚው ነጥብ በዚህ ስብሰባ ከአቅሜ በላይ በሆነ ችግር አልተገኘሁም ያለው ኤልያስ ክፍሌ ብዙውን ጊዜ የሚቀርብበትንና በአብዛኛው ለሻዕቢያ ያሳያል የሚባለውን ወገናዊነት በአንደበቱ አረጋግጡአል።” ሻዕቢያ ወያኔን ፈጥሮ ነገር ግን በወያኔ እንደ ሻዕቢያ የተጠቃ የለም” ሲል ቁጭቱን የገለጸው ኤልያስ ከሻዕቢያ ጋር በሁሉም መስክ አለመቆም “መጃጃል ነው” በማለት አጋርነቱን አስመስክሩአል። በርሱ ገለጻ ጦርነት ቢጀመርም ከሻዕቢያ ጎን መሰለፍ ከጥርጣሬ የማይገባ ነው። ይህን አቁአሙን በቃለመጠይቁ ወቅት አበበ በለው ብቻ እንደሚቃወመውና ሊከራከረው ግን እንደማይፈልግ ገልጾለታል። አበበና ኤልያስ ይህን መሰል የጎላ የአቁአም ልዩነት ካላቸው ለምን ይሄን ያህል የወያኔ ሰለባ የሆኑ መሪዎችን ለማጥቃት ተሳሰሩ ሲሉ የሚተቹም አሉ።
ቀደምሲል ባቀረብነው ዜና የስብሰባው ወጪ የተሸፈነው በኤምባሲው እንደሆነ መግለጻችን ይታወሳል። እነዚህ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት በቅንጅት መሪዎች መካከል በተፈጠረው ልዩነት በመግባት ከሚያደርጉት ተግባርና በአሁኑ ወቅት ይፋ እየሆነ ካለው ጉዳይ ጋር በተያያዘ በርካታ ገለልተኛ ወገኖች የሚያሰሙት ጥርጣሬ ጎልቶ እየወጣ ነው። በተጨማሪም ይህ ራስን የመከላከል ይመስላል ሲሉ ብዙዎች በተቹት መግለጫ ተናጋሪዎቹ እውነቱና ሊናገሩት የሚፈልጉት ሲጋጭባቸው ታይቱአል። ቀደም ሲል ታማኝ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሰታገል ማንም ከጎኔ አልነበረም” ሲል ለነጻነት ራዲዮ የሰጠውን መግለጫ የሚያስታውሱ ወገኖች በውቅቱ በኢትዮጵያ ይካሄድ ከነበረው የወጣቱ እንቅስቃሴ አኩአያ ለራሱ የሰጠውን ግምት በማነጻጸር ተገቢውን መልስ ቢያገኝ ከዚህ መሰል ስህተት ይድን ነበር ብለዋል።