ሼክ አላሙዲን ለሰሜን አሜሪካ የ2008

የዋሽንግተን የስፖረት በዓል ገንዘብይሰጣሉ!


ኢትዮጵያ ዛሬ- የያዝነው አውሮፓውያን አመት የሰሜን አሜሪካ የእግር ኩዋስ ውድድር በዋሽንተን ዲሲ ውስጥ እንዲካሄድ ከበርቴው ሼክ መሀመድ አላሙዲን ያደረጉት ተፅዕኖ ውጤት አስገኝቱዋል ተባለ። ከሰሜን አሜሪካው ስፖርት ፌዴሬሽን ባለሙዋሎች ጋር ቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ሼኩ መጪው የእግር ኩዋስ ውድድር በዋሽንግተን እንዲደረግና ቀደም ሲል ቃል ገብተው ያልሰጡትን $250,000.00 ጨምሮ ደጎስ ያለ ገንዘብ እንደሚሰጡ በወኪሎቻቸው አማካይነት መግለጣቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል። የእግር ኩዋስ ፌዴሬሽኑ የዚህን አመት በዓሉን በዋሽንግተን ለማካሄድ ሲያቅድ የውድድሩ ሜዳ RFK  ስታዲየም እንዲሆን መወሰኑ መረጃው ጠቁሙዋል። ለስታዲዮሙ የሜዳ ኪራይ ብቻ እስከ $700,000.00 የሚያስፈልግ ሲሆን ከሼኩ እርጥባን ማግኘት ወሳኝ ሆኑዋል። ለሼኩ ቅርብ የሆኑትና የሰሜን አሜሪካ ፌዴሬሽኑ የጡት አባት የሚባሉት አቶ አብነት ዋነኛ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ ግለሰብ መሆናቸውን የገለጠው መረጃ በቦርዱ ከሼኩ ጋር ግንኙነት መኖሩ የረበሻቸውን አባላት ማግባባት ይዘዋል። የመጪው የሰሜን አሜሪካ እግር ኩዋስ በዓል እንደቀደሙት ሁሉ ከፖለቲካ ነፃ በሚል የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎች የስብሰባ ማስታወቂያ እንኩዋን እንዲያሰሙ እንደማይፈቅድ ከወዲሁ የታወቀ ነው። የመጪው በዓልም ከተቃዋሚዎች የጸዳ እንዲሆን የኢአህዴግ ቁርጠኛ ደጋፊው የመሀመድ አላሙዲ ወኪሎች በቦርዱ ስብሰባ ሲያሳስቡ በግልፅ ተደምጠዋል። እነዚሁ የሼኩ ደጋፊዎች በ<ቅንጅት> መፈረካከስ የተነሳ በዲያስፖራው ውስጥ አንዳችም ተቃውሞ እንደማይቀሰቀስም ግምታቸውን ሰንዝረዋል።
በስደተኛው ትከሻ ላይ የተሰመሰረተውን ይህ የሰሜን አሜሪካ ፌዴሬሽንን ወደ ሀገር ቤት ይዘው ለመግባትና ለመንግስት እጅ መንሻ ለማድረግ የሚፈልጉ በፌዴሬሽኑ ቦርድ ውስጥ መኖራቸውንም የውስጥ አዋቂዎች ይመሰክራሉ።