ንዋይ ደበበም እንደ ሰለሞን ተካልኝ?
"ሀገሬ ሰው አጣሽ ወይ?"ን- ያዘፍናል!

ኢትዮጵያ ዛሬ የኢትዮጵያ የመንግስት ተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ከባዶ ስም በስተቀር የፖለቲካ ብስለት በሌላቸው <አርቲስቶች> እጅ መውደቁ ከቀን ወደ ቀን የመከዳት አደጋውን አክፍቶታል። ሰው የሌለበት በሚመስለው በዚህ የተቃወሚዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የ<መፈክር ሰዎች> ሆነው ከመድረክ የታዩት አርቲስቶች በአንድ አዳር ፈልሰው ለገዢው ሳይጠየቁ እጅ መስጠት ከጀመሩም ሰንብተዋል። በተቃዋሚነት አለሁ ያለውና እስከአስመራ ተጉዞ የአቶ ኢሳያስ አፈ ወርቂን እጅ የሳመው ሰለሞን ተካልኝ ወዲያው ኢህአዴግን ደግፎ ለመናገር ሲደፍር ብዙዎችን አስደንግጦ ነበር።

የሰለሞን ተካልኝን ክህደት ሲያወግዙ ከነበሩት መካከል ታዋቂው ዜመኛ ንዋይ ደበበ አንዱ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን በቅርቡ በይፋ በሰጠው ቃለ ምልልስ ወደ ሀገር ለመግባት የሚያመቻች መንገድ ለመጥረግ መሞከሩን ታዝበናል። ንዋይ ደበበ በምርጫ 97 ከወዳጁ ታማኝ ቤት ውስጥ የቅንጅትን ምልክት (በቪ መልክ) እያሳየ የተነሳው ፎቶግራፍ አዲስ አበባ ለአርቲስት ደበበ እሸቱ እንዲደርሰው በማድረግ ለሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ኢትዮጵያውያን መካከል ሲበተን እንደነበረ አይዘነጋም። ዜመኛው ንዋይ የወቅቱን ዝና በፀጋ የተቀበለው ቢመሰልም የ<ቅንጅት> መሪዎች ከወህኒ በዋሉ ማግስት - <እርሱ ሳይፈቅድ የተነሳው ፎቶግራፍ> እንደሆነ በመግለፅ በአደባባይ ሲናገር ያደመጡት ይመሰክራሉ።

በዋሽንግተን አካባቢ አዲስ በታተመ ጋዜጣ ላይ ንዋይ ለመሰደዱ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው የ"አንድ የሕዝብ ሀብት የሆነው ጥላሁን ገሰሰ አንገቱ ላይ አደጋ በደረሰበት ወቅት ህዝብም መንግስትም በማን አለብኝነት ስለጉዳዩ መፍትሄ ሳይሰጡት ስላለፉት የሚቀጥለው አደጋ" እንዳይደርስበት "አርቆ በማየቱ" መሆኑን በድፍረት ተናግሩዋል። የአሜሪካ መንግሰት የፖለቲካ ጥገኝነት ለዜመኛው ንዋይ ከ<ጥላሁን ገሰሰ አንገት አደጋ> ጋር አያይዞ ሰጥቶት ይሆን? የሚል የፌዝ ጥያቄ የሚያነሱም ላይጠፉ ይችላሉ። <አርቲስቶቹ> ምንም ሳይናገሩ፤ ሻንጣቸውን ይዘው መሄድ ሲችሉ <አስለፍልፍ ተክልን> የበሉ መምሰላቸው የሚያሳዝን ነው ያሉንም ብዙ ናቸው።