ለመለስ ዜናዊ የተቃጣው ጥይት ሌላውን በላ |
|
![]() |
መለስ ዜናዊ |
ኢትዮጵያ ዛሬ፡ በመለስ ዜናዊ ላይ ግድያ ለማካሄድ እንደሆነ በተነገረለት የተቀነባበረ የሽምቅ ጥቃት ሁለት ወታደራዊ አጃቢዎች መገደላቸው ተሰማ።
ስለ ጥቃቱ የአካባቢውን መረጃዎች በማሰባሰብ ለመረዳት እንደቻልነው የግድያ ጥቃቱ የተካሄደው መለስ ዜናዊ ትግራይ ላይ የህወሓትን የምስረታ በዓል አክብረው ወደ ጎንደር ሲመለሱ ጠብቆ የተቀነባበረ ነበር ተብሉአል። መለስ በዓሉ ከተከበረበት ሽሬ በመኪና ወደ ጎንደር ይሻገራሉ የሚል መረጃ ሸማቂዎቹ ሳይደርሳቸው እንዳልቀረ ታውቁአል። በዚህ መረጃ መሰረትም ሸማቂዎቹ በተባለው ሰዓት በመጡት መኪኖች ላይ ያዘጋጁትን ጥቃት ፈጽመዋል። ይህ ጥቃት ሲደርስ በወቅቱ መለስ ያሉበት ቡድን ሳይሆን ቀደም በሎ ያካባቢውን ሁኔታ ለመቃኘት የተንቀሳቀሰ ቡድን እንደሆነ ሰለጥቃቱ የገለጹት የዜና ምንጮቹ ገልጸዋል።
በወቅቱም ሁለት የሚደርሱ ወታደራዊ ባለስልጣናት ሞተዋል ተብሉአል። ጥቃቱ የተፈጸመበት ሰአት ምሽት እንደነበር ሲመለከት የተኩስ ድምጹን ተከትሎ ወዲያውኑ በርካታ ቁጥር ያለው ወታደራዊ ኃይል ቦታውን በመቆጣጠር የጥቃቱ አድራሾችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሙከራ አድርገዋል። ጥቃቱ የተፈጸመባት ወርቀ ደቦ በመባል የምትጠራው ቦታ በአምባ ጊዮርጊስና በገደብዬ መሃል የምትገኝና ጥሩ ወታደራዊ መሬት በመሆኑዋ ጥቃቱን የፈጸሙትን ለመያዝ የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካ የዜና ምንጫችን ገልጹአል።
ይህንን ተከትሎ የመንግስት ወታደሮች በወሰዱት ርምጃ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ተይዘው መታሰራቸው ታውቁአል። ድርጊቱ ከተፈጸመበት የካቲት ወር አጋማሽ አንስቶ እስካሁን ድረስ ፍንጭ አለመገኘቱ ባለስልጣናቱን አስጨንቆአቸዋል ተብሉአል። የኢትዮጵያ ዛሬ፡ዝግጅት ክፍልም በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል። በተለይም የሞቱትንና ታስረው የሚገኙትን ማንነት ለማጣራት የምናደርገው ጥረት ይቀጥላል።
ከዚህ በተጨማሪ ከግድያው ሙከራ በሁአላ ከጎንደር ዙሪያ ወደ ከተማው የሚገቡ የአካባቢው ነዋሪወች ከፍተኛ እንግልት እንደሚደርስባቸው እንድ የአምባ ጊዮርጊስ ነዋሪ በቦታው ለተገኘው ለዚህ ዜና ዘጋቢ ገልጠዋል ።