አቶ በድሩ አደም በዶ/ር ታዬ ምክንያት በኢንጂነር ሀይሉ ላይ ሊዘምቱ ነው፤


ኢትዮጵያ ዛሬ--ማብቂያ ያጣው የቅንጅት መሰነጣጠቅ በአቶ በድሩ አደም ከሌላ ዙር ሙግት ውስጥ ሊገባ ነው። <የቅንጅቱን ሊቀ መንበር ኢንጂነር ሀይሉን ለመደገፍና በዶ/ር ብረሃኑ የሚሸረበውን ሴራ ለማጋለጥ> መምጣታቸውን ሲናገሩ የሰነበቱት አቶ በድሩ አደም ከአሜሪካ ቆይታቸው በድንገት ወደ አዲስ አበባ የመመለሳቸው እውነታ <ልዩነት አለኝ> በሚል እንደሆነ ሰሞኑን "ተቃውሞዬን ካላሰማሁ" በሚል የወያኔን ጋዜጦች ሳይቀር በራቸውን እየቆረቆሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አረጋግጠዋል።
አቶ በድሩ አደም በቆይታቸው ከኢንጂነሩ ጋር ያጋጫቸው በ<ሰሜን አሜሪካ በምክር ቤትነት የተዋቀረውና በዶ/ር ታዬ የሚመራው አካል ላይ ባላቸው ቀጥተኛ ተቃውሞ እንደሆነ ታውቁዋል። ዶ/ር ታዬ አቶ በድሩን ቀደም ሲል በ<አፍቃሬ ወያኔነት> ሲወነጅሉዋቸው መቆየታቸውን አስታውሰው ለጊዜው የተረሳ የሚመስለውን <መጠላላት> የቀድሞው የሰሜን አሜሪካ የቅንጅቱ አመራር ሊቀ መንበር ሻለቃ ዮሴፍ ያዘውና ነዋሪነታቸው ካሊፎርኒያ የሆኑት ኢንጂነር ሞገስ ለነርሱ በሚጠቅም መልኩ የቆሰቆሱዋቸውና ያስነሱዋቸው መሆኑን ውስጥ አወቂ ምንጮች ገልጠዋል።
ኢንጂነር ሀይሉ ሻወል በሰሜን አሜሪካ ክፉኛ ተጠልተዋል የተባሉትን ሻለቃ ዮሴፍ፤ ኢንጂነር ሞገስና ሌሎችንም ማግለል መያዛቸውና በነርሱ ምትክ ዶ/ር ታዬን፤ አቶ አሰፋ ደርሰህንና የመሳሰሉትን ከማቅረባቸው ጋር የተያያዘ መጉዋተት አቶ በድሩን አደምን ጠለፎ እንደወሰዳቸው ታውቁዋል። አቶ በድሩ አደም በፋይናንስ በኩል የ<ሻለቃው ወገን> ጥቂት እንደረጠባቸው የሚገልጡም አሉ። አቶ በድሩ አደም ማፈሪያ በሆነው የመሰነጣጠቅ ሂደት ውስጥ ሌላ <ጉዳይ> ይዘው ወደሌላ ሙግት ለመግባት የያዙት ጎዳና ምን ለፖለቲካው ይፈይድ ይሆን? የሚል ጥያቄን በሚያውቃቸው ወገን አስነስቱዋል።
በነገራችን ላይ አቶ በድሩ በአሜሪካ <እንኩዋንም ቅንጅት ስልጣን አልያዘ> ሲሉ የተናገሩትን ገዢው ፓርቲ ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ እያዋለው ነው።